ከስዩም መስፍን ጋር በአንድ በረራ (ጀግና ደግ፣ ፈሪ ጨካኝ)

Post Reply
africangear
Posts: 396
Joined: Fri Dec 11, 2020 5:07 pm

ከስዩም መስፍን ጋር በአንድ በረራ (ጀግና ደግ፣ ፈሪ ጨካኝ)

Post by africangear »

Seyoum-Mesfin.jpg
በግእዙ 1986 ይመስለኛል፤ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የመጓዝ ዕድል ገጥሞኝ ነበር። መዳረሻችን ሳውዲ አረቢያ ነበር። አውሮፕላኗም የሳውዲ ንጉሳውያን ነበረችና ግዙፍ ባትሆንም በጣም ምቾት ነበራት። የወንበሮቹ አቀማመጥ ራሱ የሳሎን ቤት ዓይነት ነው። እኔ የጉዞው አካል የሆንኩበት ምክንያት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሆኜ፣ የውጭ ጉድይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ወክለው የሚከውኑትን ዲፕሎማሲ ለመዘገብ ነበር። አብረውኝ ሁለት ካሜራማኖች ነበሩ። አንዱ ኢሳያስ ለማ (አፈሩን ይቅለለው)፣ ረዳቱ ሰሎሙን እንዳለም አብረውኝ አሉ።

ሪያድ ሁለት ቀን ቆይተን ወደ ጅዳ ሄድን። ሁለቱም ጋር ያረፍነው ምቾት ያለው የመንግስት እንግዶች ማረፊያ ሆቴል ነው። በአንድ አጋጣሚ ከተማውን ቀርጸን ወደ ሆቴላችን ስንመለስ ሚኒስትር ስዩም ጋር ሊፍት ውስጥ ተገናኘን። እኔና ሰለሙን በእጅ እየጨበጠ ሰላም ካለን በኋላ ኢሳያስ ለማ ጋር ደርሶ እጃቸው ሲነካካ የኤሌክትሪክ ንዝረት ተሰማቸውና ሁለቱም ደነገጡ። ይህ አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ይመስለኛል። ያ ኢሳያስ ለማ ግን እንደምንም አጠማዝዞ፣ ከዚያች ሁሌ የሚነግረን ጉዳዩ ጋር አገናኛት። ክፋቱ ደግሞ በሊፍት ልታልቅ የምትችል አጭር ወግ አልነበረችም። አይ ኢሳያስ!

“ለምን መሰልዎት ክቡር ሚኒስትር፣ እኔ ድሮ ጃንሆይ የቤተ መስንግስት ደረጃ ሲወርዱ ከፊለፊታቸው የኃሊት እየሄድኩ ስቀርጻቸው፣ የካሜራው ገመድ አደነቃቅፎኝ በጀርባየ ወድቄ በጣም ተጎዳሁ። አከርካሬ ተዛባ። በጃንሆይ ድጋፍ እስራኤል ሂጄ ታክሜ ነው የዳንኩት። ነገር ግን አሁንም ጀርባየን እንዲደግፍ የገባብኝ የብረት ዘንግ አለ። እና እሱ ነው አሁን ስጭብጥዎት ኤሌክትሪክ የፈጠረው።” ስዩም የሰማውን ያመነ አይመስልም። ግን ይቀበለው አይቀበለው ሳያስብቅ፣ “ነው?” እያለ ለማስጨረስ ኮሪደሩ ላይ ትንሽ ቆም አለለት። በጨዋ አንደበት አለፈው። ኢሳያስ ይህችን ታሪክ ለመናገር ማንኛውንም ሁኔታና አጋጣሚ ይጠቀማል። ተው ተብሎም አልሰማም።

ጅዳ ላይ በቀጣዩ ጥዋት የት እንደሄደ ሳናውቅና ሳይነገረን ቀረ። ስለዚህ ዝም ብለውን የከተማዋን አንድንድ ተጨማሪ ገጽታዎች ቀርጸንና ጥቂት ተላላፊዎችን ጠይቀን ተሎ ተመለስን። መኪናም ብርም ስላልነበረን ከተማዋን በደንብ ተዘዋውረን ለመጎብኘት አልዳዳንም። አቶ ስዩም ከሄደበት ሲመለስ ሎቢው ጋ ተቀምጠን አየን። ትንሽ ቆም ብሎ፣ ወደ እኛ እያየ ለኛ የማይሰማ ነገር ተናገረውና ወደ ሊፍቱ ሄደ። ጠባቂውም ወደኛ መጣና “አቶ ስዩም መኪና ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጥራላቸውና ከተማዋን ያሳዩዋቸው፣ ብሎኛልና አሁን ልጠራላቹህ ነው፣ ተዘጋጁ” ይለናል። ኢሳያስ ደፈር ብሎ “ከተማዋን በባዶ ኪስ ምን እናረጋታለን?” ሲል በግልጽ ተናገረ። ይሁን እንጂ አልቀረንም። ተያይዘን ልንወጣ ስንል፣ እንደገና የስዩም ጠባቂ መጥቶ፣ “ለሶስታቹህ” በማለት ሚኒስትር ስዩም ሁኔታችንን አይቶና አዝኖ የላክለንን 300 ዶላር አስታቀፈኝ። ከዚያ በኋላ የኢሳያስ ምርቃትና ውዳሴ ማቆሚያ አልነበረውም።

ከጊዜ በኋላ፣ ጽናት የተሰኘ የሃይላይ ሓድጉ መጽሃፍ ታትሞ ወጣ። መጽሃፉ በስዩም የትግል ታሪክ ዙርያ ያጠነጥናል። እዚያ መጽሃፍ ላይ ለማጉላት የተሞከረው ግለ-ስብእና የስዩም ደግነትና ጀግንነት ነው። የስዩም አደጋዎችን ያለ ፍርሃት የመጋፈጥ ወኔውና ለጓዶቹ የነበረው ርህራሄ በሰፊው ታይቷል። ጭንቅላቱ በጥይት ተመቶ ጥይቷ መውጣት ነበረባት። ለማስወጣት ደግሞ የራስ ቅሉ መከፈት የግድ ሆነ። ማደንዘዣ ግን አልነበረም። ታጋይ ሃኪሞች “ስቃዩን አትችለውም” ቢሉትም “አድርጉት” አላቸው። አደረጉት። ለህዝብ የነበረው ፍቅር ወደር የለውም። የብዙ አገሮች ወዳጆች ቢኖሩትም በውጭ ድርጅት ተቀጥሮ መስራትን አልፈቀደም። መሰደድም እንዲሁ። ስዩም፣ የጀርባ ቋሚ ህመም የሚያሰቃየው አዛውንት ነበር። ለዚህም አልተበገረም።

ስዩም፣ አፍሪካና ኢትዮጵያ የሚገለገሉበት ብዙ አዳዲስ የዲፕሎማሲና የሰላም ሃሳቦች አቅርቦ ለፍሬ እንዳበቃ የውጭ ምሁራን እየመሰከሩ ነው። ኢትዮጵያም አፍሪካም በስዩም ጊዜ ከፍ ከፍ እያለች ነበር። የኢትዮጵያ ገጽታም በጎ ምስል እየያዘ ነበር። “መግደል መሸነፍ ነው” ሲሉን የነበሩ ሰዎች የአዛውንቱን ህይወት በጭካኔ ለህልፈት አበቁት። ሃሳቡ የህዝቡን ቅስም የምንሰብረው በዚህ መልክ ነው ከሚል እሳቤ ነው። ውጤቱ ግን ተቃራኒ ሆነ። ስዩምን የበለጠ በያንዳንዱ ሰው ልብ ላይ አነገሱት። ቀጥሎ፣ በትግራይ ምድር ስዩም በሚል ስም የሚጠሩ ልጆች ቁጥር ይበረክታል።

ስዩም ህያው ነው!


Post Reply