የአዲስ አበቤው የዛሬ ውሎ
ነሓሴ 5 ቀን 2013 ዓ.ም
"ብርቱካን በልቼ ሎሚ ሎሚ አገሳኝ፤ ምክርሽ አይደለም ወይ ዝናሽን ያስረሳኝ" አለ አዝማሪው፡፡ እናንተዬ፤ ዛሬ አዲስ አበባ ወሬው ሁሉ፤ "እባብና ዘንዶ" ቢሆንብኝ ጊዜ፤ የዛሬዋን ቀን ስፖንሰር ያደረገው የደንና የዱር አራዊት ሚኒስተር ነው እንዴ ብዬ ነበር፡፡
ግራ ቢገባኘ ይሄ ነገር ምንድነው ብዬ ብጠይቅ፤ ለካስ አዲስ አቤቤው ሁሉ ዓይኑን እያፈጠጠ የሚያመሸው "የእነ በሎም ቲቪ" ላይ ነው አሉ፡፡ ለነገሩ እኔም አልፎ አልፎ ከሰኞ እስከ ሰኞ እመለከተዋለሁ፤ ምርኮኛውን ባየሁ ቁጥር ግን ያበሽቀኛል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ሬንጀር የለበሰ ወታደር ስመለከት፤ ምርኮኛ የሚመስለኝ ግን እኔን ብቻ ነው?
"ወታደሩ ሁሉ ምርኮኛ ሆነ አይደል እንዴ" ያልኩት ጓደኛየ ምን ቢለኝ ጥሩ፤ "ህዝቤ ብልጥ ነው እባክህ፤ እነ ብርሃኑ ጁላ በምርኮ የደረሱበትን የብልፅግና ከፍታ አይተው፤ እንደባለፈው ብአዴንና ኦህዴድ ሆነን ተመልሰን ኮርቻ ላይ እንወጣለን ብለው ነው" ብሎ ፈገግ አሰኘኝ፡፡
የአምነስቲ የሰቆቃ ሪፖርት፤ የትግራይ እናቶችንና ልጃገረዶችን ስለደፈሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮችና ሚሊሻዎች ባለ ብዙ ገፅ ሪፖርት፤ ገና ከማለዳው ብጣድበትም፤ ጨርሼ ለማንበብ ዓቅም አነሰኝ፤ አልቻልኩም፡፡ በኢትዮጵያዊነቴ አፈርኩኝ፤ አንገቴን ደፋሁ! ይኸን እንዲተገብሩ ያዘዘውንም የፈፀመውንም ለቃቅሞ መሸኘት፤ ፍትህን ማጠንከር እንጂ ሕግና ሰብኣዊነትን ማዛባት አይመስለኝም ብዬ አሰብኩኝ፡፡
ለነገሩ የእነዚያ የትግራይ እናቶችና ልጃገረዶች፤ ልጆችና ወንድም እህቶች፤ "ዘመቻ ፀሐይ መውጫ" ብለው እየመጡ አይደል! ያኔ ድሮም "ዘመቻ ፀሓይ ግባት" ብለው ነበር ሻቢያን እጅ ወደላይ አሰኝተው በአስር ጣቱ ያስፈረሙት፡፡
የአምነስቲን ሪፖርት ሳነብ ይበልጥ መንፈሴን ያወከው፤ የነ ሙፍሪያት ሳህለወርቅ መዓዛ ብርቱካን እና ሌሎች አጋንንት የብልፅግና ሹመኛ ባልቴቶች ገፅታ እየታየኝ፤ ምንኛ ሰባዊነት ያልፈጠረባቸው መሆናቸው ሰቀጠጠኝ! ይህንን ድርጊት በሴትነታቸው ሊያወግዙት አይደለም አባሪ ተባባሪ መሆናቸውንና፤ በፆታዊ ጉዳይ ስም የተለያየ ተቋማተ መስርተው ዶላር መቀራመታቸውን ሳስብ፤ ውስጤ ደማ! እንስት ሆነው ፀረ-እንስት እናት እህቶቻቸው በመሆናቸው ውስጤ ክፉኛ እንደተረበሸ፤ የታክሲ ወረፋየ ደርሶ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ገባሁ።
ከታክሲው ሬዲዮ የሚሰማው ሁሉ፤ የተጋደመውን የአዲስ አበቤን ስሜት ይበልጥ የሚጫጫንና የሚያስተኛ፤ እንክተት ወይስ እንንቀል የሚለውን ብዥታችንን የበለጠ የሚያባብስ ነበር። በታክሲው ውስጥ ያለነው 13 ተሳፉሪዎች ብንሆንም፤ ከሬዲዮው በስተቀር ማንም ከማንም ጋር አያወራም ነበር፡፡ "ቼ በለው፤ እረ ቼ በለው!" በሚለው የቀረርቶ ሙዚቃ ታጅቦ፤ "የጥሙጋ ወረዳ ነዋሪዎች ወደ ብርሸለቆ ማሰልጠኛ እየጎረፉ ነው፣ የደሴ አስተዳዳሪዎች አሸባሪውን ለመፋለም ጥሪ አደረጉ፣ የሰበታ አስተዳዳሪ ከነዋሪው የሰበሰቡትን ባለሻኛ በሬዎች ለመከላከያ አስረከቡ፣ የጅማ በሬዎችን ዛሬ መከላከያ ተረክቧል" ይላል ሬዲዮው ሳይታክት፡፡
ሬዲዮው በሙዚቃ ጣልቃ ቀጠለና፤ "ወልቂጤ ለመከላከያ በድጋሚ በሬ አዋጡ ..." ሲል፤ ከፊታችን የተቀመጠው ጎልማሳ ንዴት ባዘለ ቅላፄ፤ "ምን በሬ በሬ ይሉናል፤ እነዚህ ሰዎች ሰራዊቱን ጨርሰው፤ በቀንድ ከብት መዋጋት ጀመሩ እንዴ?" ብሎ ዝምታውን ሰበረው፤ ሳቅ ባይገኝም፤ ተሳፋሪው ትንሽ ፈታ ፈገግ አለ፡፡ አዲስ አበቤ እኮ አፍ መፍታት ታቴ ታቴ ማለት እየጀመረ ነው፡፡
"እንዴት ነው ነገሩ! ከገባን ጀምሮ ሬዲዮኑ እኮ ስለጦርነት ነው የሚያወራው፤ ምነው ጎበዝ ሳናውቀው ጣሊያን ገባች እንዴ? የሀይማኖት አባቶች፣ ምሁራን ሁሉም የሚያወሩት ስለ ጦርነት እና ገሎ ስለመጨፈር ሆነሳ! እብድ ቤትዋን አቃጥላ፤ "አሁን በራልኝ እልልልልል…" አለች አሉ፡፡ ሀገሪቷ ምን እየሆነች እንዳለች እረ የተረዳነው አልመሰለም" አለ ይኸው ጎልማሳ፡፡ ተሳፋሪው ግን አላመነውም፤ የበለፀገ ተናግሮ አናጋሪ ነው በሚል፤ በዝምታ የጎሪጥ አየነው፡፡
"እንዴ ጁንታው እኮ ነው አገራችንን እያተራመሰ ያለው" አለ፤ የታክሲ ረዳቱ፡፡ "የምንበላው ዳቦ እንኳን አጥተን በዳቦ ሰልፍ በዝናብ ሰዓታት እንፈጃለን! ጁንታው አይቅናሽ" አለ ረዳቱ እርግማን ጨምሮበት::
"እና አንተ ወጠምሻ ነህ፤ ከመራገም ታዲያ ለምን አትዘምትም?" ቢለው ያ ጎልማሳ፤ ረዳቱ የዋዛ አልነበረምና፤ "እኔ ከሄድኩኝ እናንተን ታክሲ ማን ያመላልስ" ብሎት እርፍ፡፡
ከኋላችን የተቀመጠው ጢማም መልከ መልካም ጎልማሳ ጣልቃ ገባና፤ "አረ ለመሆኑ፤ ጁንታውን አጎትክ እንደ ዱቄት በትነነዋል አላለም እንዴ?" ቢለው ረዳቱን፤
"ውይ ጋሼ እሷ ነግራው ነዋ"
"ማናት እሷ ደግሞ?"
"አረ ጋሼ፤ አገሪቷን የምትመራዋ ናታ" እንደ መቅለስለስም ያምረዋል፤ አናቱን እያሻሸ፡፡
"ፕሬዝዳንቷን ማለትህ ነው?"
"ፕሬዝዳንቷማ እንደ እግር ኳስ የመስመር አራጋቢ ዳኛ፤ ቀይ መስመር ከማስመርና እራት ሲኖር ድክድክ እያለች ከመጋበዝ ውጪ ምን ታውቅና"
"እና፤ እሷ ታዲያ ማን ናት?
"እሷ ማናት? ብለው አንዳንድ የአዲስ አበባ ኑዋሪዎች ግምታቸውን እያስቀመጡ ነው፡፡ እና ጋሼ የአንተስ ግምት ማን ትመስልሃለች?" ጥያቄን በጥያቄ፤ ረዳቱ ነው፡፡
"ባለቤቱ ዝኑ እንዳትሆን?" ያ መልከ መልካም ጎረምሳ፤
"እሷማ የዘንዶ አጫዋች ሆና፤ ዘንዶውን አጋድማብን ማለፊያ አሳጣችን እኮ!"
"አንተ ሰውዬ፤ የምታወራውን አታውቅምና ሊገባኝ አልቻለም" ቢለው፤
"ኣቦ ተወን! ሳልበለፅግ በድህነቴ ልኑርበት፤ ብዙ አታናግረኝ፤ ብርቱካኔን ልብላበት" ብሎ አስቀይሶ "እዚያጋ ሒሳብ" ይል ጀመር፡፡
መልከ መልካሙ ጎልማሳ እንደመብሸቅ አሰኝቶት፤ "አንተ እራስህ እባብ ዘንዶ ነህ የምትመስለው!" አለዉ፡፡
ረዳቱም ዋዘኛ አልነበረም፤ "እንደ ሰውየው እባብ ከመሰልኩማ፤ ራስ ራስን መቀጥቀጥ ነዋ!"
"ሊቀጠቅጡት ተቃርበዋል አለ" ሌላኛው ተሳፉሪ
"ታዲያ ዱላ በማቀበል እንተባበራቸዋ!" ቢል መልከ መልካሙ፤ እንደ እኔ ጆሮውን አጥግጎ ሲያዳምጥ የነበረው ሌላ ፈርጠምጠም ጠቆር ዓይኑ ቀላ ያለ ተሳፋሪ ቀበል አደረገና፤ "ምነው ጃልመሮን ካልሆንኩ አልክ" አለው በንዴት፡፡
"እንዴት?" ቢል መልከ መልካሙ፤
"አገራችንን ሁሌ የሚያጠቃት የውስጥ አርበኛ ነው! አየህ እንዳንተ ዓይነቱ የእናት ጡት ነካሽ በበዛበት አገር ውስጥ፤ የተዳከምን ስለመሰላቸው፤ አሸባሪዎቹ ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ተባብረው፤ አዲስ ጋብቻ ፈጥመው ዘመቱብን" አለ በንዴት፤ ጠንከር ያለው ብልፅግና ነው፤ ፊቱ ሁሉ ግሎ ቀልቷል፡፡ ያ የፍርሃት በሽታየ ተቀሰቀሰብኝ፤ ሽሽ ሽሽ አለኝ፤ ያለ ቦታየ ብወርድም በወደድኩ፡፡
እኔ በፍርሃት ስናጥ፤ መልከ መልካሙ ዘና ብሎ፤ "ብሮ! ምን አዲስ ነገር ተገኘ! ላለፉት ሶስት ዓመታት አብረው እየሰሩ ነው ስንባል አልነበር እንዴ፡፡ እኛስ ከአስመራው ሰውዬና ከሌሎች ባዕዳውያን ጋር አብረን ተባብረን፤ የራሳችን ወገን በሆነው የትግራይ ሕዝብ ላይ አልዘመትንም እንዴ! ዛሬ ላይ ደርሰን አዲስ ጣምራ ግንኙነት ፈጠሩ ብለን ማልቀሱ አይነፋም፡፡ ሰው ላይ የጭቃ ስም መለጠፉ ደግሞ ያቅለሸልሻል፤ ይህች አገር የጋራችን መሰለችኝ" በቅባት ርሶ ጀርገግ ያለውን ጢሙን እያፍተለተለ፡፡
ከዚህ በላይ አልቻልኩም፤ የውስጤ ፍርሃት ናጠኝ፤ ቅቤየን ሊያወጣው ምንም አልቀረውም፤ ጆሮየ ነው ደግሞ ቀድሞ የሚያልበው፡፡ ለክፉም ለደጉም አስቀድሞ ማምለጥ ይበጃል፤ ያለመዳረሻየ፤ "ወራጅ አለ" ብለው ረዳቱን፤ "ምነው ጀለስ፤ ያለቦታሽ፤ ፍንጣሪ ተባራሪ ወይንስ እባቡን ዘንዶውን ፈራሽ እንዴ" እያለ አወረደብኝ፡፡
ከተጠየቅሁ አይቀር ብየ፤ ድምፄም ውጣ አልወጣም እየተናነቀኝ፤ "ወዳጄ እባቡ ከሚነድፈንና ዘንዶው አፉን ከፍቶ ከሚሰለቅጠን፤ ቀድሞ መሸሽ ትውልድን አያድንም ትላለህ!" ብዬ ወረድኩኝ። ቀሪውን መንገድ በሰላም በእግሬ ተያያዝኩት፡፡
አዲስ አበቤው ነኝ፤ የነገ ሰው ይበለን!