የአዲስ አበቤው የዛሬ ውሎ - ነሓሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም

Ethiopia related news and publications
Post Reply
africangear
Posts: 404
Joined: Fri Dec 11, 2020 5:07 pm

የአዲስ አበቤው የዛሬ ውሎ - ነሓሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም

Post by africangear »

የአዲስ አበቤው የዛሬ ውሎ
ነሓሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም

"መጨረሻው ግን የት ነው?" ይለኛል፡፡ ሁሌ ቅዳሜ ቅዳሜ ስንገናኝ፤ ከሰላምታ ቀጥሎ የጓደኛየ መነሻ ጥያቄው ነው፡፡ ከምር፤ ሁሌ ስለፖለቲካ ማውራት፤ እኔ እንኳን ስልችት ነው የሚለኝ፡፡ እሱ ግን የ1980ዎቹ ትውልድ አይመስልም፤ ልክ እንደ እነኣባየ ነው፤ ኝኝ እንዳለ ነው፡፡

ሳምንቱን ሙሉ በዓለምአቀፍ ሆነ በማሕበራዊና በሰፈር ሚዲያ ያየውን የሰማውን ሁሉ፤ ቅዳሜን ጠብቆ የሚዘረግፈው እኔ ላይ ነው፡፡ ካልተነፈሰ የሚያመው ስለሚመስለኝ፤ እያዘንኩለት ባላዳምጠውም እሰማዋለሁ፡፡

"በእኛ ትውልድ ዘመን ይህን ዓይነት የ21ኛው ክፍለዘመን አሰቃቂ ግፍ ሲፈፀም፤ ተጠያቂዎቹ የበለፀጉት ብቻ ሳይሆኑ፤ እንደ ትውልድ እኛም ተጠያቂዎች ነን!" ሲለኝ፤ "የትኛውን ነው ደግሞ?" ከማለቴ ቀጠለ፤ ከጀመረ ማን ሊያስቆመው፤ አራት ነጥብን አያውቅም፡፡

"እነ ባጫና አብቹ ዛሬም አፋቸውን ሞልተው፤ እነሮይተርስንና ኣጃንስ ፍራንስ ፕሬስንም እንደ ፌስቡከሮች አትስሟቸው ሊሉን ይሆን?" ሲል አቋረጥኩት፡፡ "በሞት አፋፍ ላይ ያለን ሰው አታንሳ፡፡ ባጫ በአደገኛ የልብ ሕመም በአገር ውስጥ ሕክምና ሊያግዙት ስላልቻሉ፤ ከሓምሌ 20 ጀምሮ በኢምሬት አገር የአልጋ ቁራኛ የሆነን ሰው እዚህ አታነሳ" ስለው ተቆጣ፡፡

"ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ ፆታ ዕድሜ ሳይለይ፣ እየተጨፈጨፈ በተከዜ ወንዝ ውስጥ እየተጣለ፤ ከአዞ የተረፈው አስከሬን በሱዳን ምድር እየተንሳፈፈ፤ በዓለምአቀፍ ሚዲያዎች በስፋት እየተዘገበ፤ አንተ ስለአንድ የአብቹ አጫዋች ትተርካለህ?" ገሰፀኝና ቀጠለ፡፡

"እስኪ ልጠይቅህ፤ እውነት እነዚህ ሰዎች ይህችን አገር ለነገ የሚፈልጓት ይመስልሃል?" ለስሙ ነው ልጠይቅህ የሚለው እንጂ አንድም ቀን እንድመልስ ዕድል ሰጥቶኝ አያውቅም፡፡ ከሰፈር ከልጅነታችን ጀምሮ እንዲሁ መድረክ እንደሚወዱት ነው፡፡ ዛሬም አደረገው፤ ልጠይቅህ ብሎ እራሱ ቀጠለበት፡፡

"ባለፈው የሕግ ማስከበር ብለው፤ የኤርትራንና የሌሎች ባዕዳውያን መንግስታትን ሰራዊት ትግራይ ላይ አዝምተው፤ የጦር ወንጀል ፈፀሙ፡፡ እነዚህ ምን ዓይነት ጉዶች ናቸው ብሎ፤ የዓለም ማሕበረሰብ ፊቱን አዞረብን፡፡ በዚያ አሳፋሪ ተግባራቸው አፍረው፤ በሰላም ድርድር ቀሚስ ውስጥ እንዳይደበቁ፤ ይባስ ብለው መከላከያውን አስጨርሰው፤ በመከላከያው ያልቻሉትን ሃይል በፖሊስና በሰፈር ሚሊሽያ እንሞክረው ብለው ህዝቡን እያጫረሱት ነው፡፡ አሁን ደግሞ በመላ አገሪቱ ውስጥ የትግራይ ተወላጆችን ማሳደድ ማጎር ድርጅቶቻቸውን መዝጋት፤ እውን ይህችን አገር ለነገ የሚፈልጓት ይመስልሃል?" ጥያቄውን ደገመው፤ እኔም ዝም፡፡

እንዲሁ እንደጨሰ ጨው በረንዳ ደረስን፤ እሱ የሚፈልገው ዕቃ ነበር፡፡ ሳምንት ከነበረበት ዋጋ ዕቃው ሁሉ በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ነጋዴውን "ምነው ባለፈው ሳምንት ይሄንኑ ዕቃ ገዝቼ ነበር፤ ከምኔው ተወደደ?" ብለው፤ "ወንድሜ እዚህ አገር ‘ከምኔው ከምኔው’ የሚለው የዛች ሙዚቀኛ ነጠላ ዘፈን ከተለቀቀ ጀምሮ፤ አገር ስትፈርስም ሁሉም ነገር ‘ከምኔው’ ሆኗል፡፡ ገዢው ሁሉ እየመጣ ‘ከምኔው’ ይለናል፤ ከእናንተ በፊት የመጡት ደንበኞች ‘ከምኔው’ ብለውን ነው የሄዱት" ብሎ ፊቱን አዞረብን፡፡

"እውነታቸውን ነዋ፤ እንዲህ ከመቅፅበት ሲጨምር፤ ‘ከምኔው’ ካላሉ፤ ምን ሊሉ ነው ታድያ" አቋረጠኝ፡፡

"አየህ ወንድሜ፤ ዕቃው የናረው በዶላሩ ምንዛሬ ነው፡፡ ዛሬ አንድ ዶላር 70 ብር ከሆነ ነገ ደግሞ 75 ብር ገብቶ ያድራል፡፡ ለዚህ ነው ዕቃ የተወደደው፡፡ ከነገ ወዲያ ደግሞ መቶ ሲገባ፤ እጃችንን በአፉችን ላይ ጭነን፤ የለውጡን ፍሬ እናጣጥማለን፡፡ እንግዲህ አላህን ፈርተው ምንዛሬውን ካላወረዱልን" ከማለቱ ወዳጄ ከአፉ ቀማው፡፡

"እነማን ናቸው የሚያወርዱላችሁ? ብሔራዊ ባንክ ነው?" አለው፡፡

"ያው እንደዛ በላቸው፤ ሁሉም እኮ በየቤታቸው የግል ብሔራዊ ባንክ አቋቁመዋል" ሲለን ከጓደኛዬ ጋር ተያየን፡፡ "እነማን ናቸው?" ቢለው ደግሞ፤ "ሞኝህን ፈልግ፤ ማንን ለማናገር ነው! የሑመራ ሰሊጥ ነጋዴዎቹን እነ በላይነህ ክንዴና ጓደኞቹን፤ ወይንም ለአብቹ የጦር መሳሪያ የሚያጋዙትን እነ ሽመልስ ክንዴና ኤሊያስ ጀማል ከነጓደኞቻቸው፤ እንድልህና ፖለቲካ ተናገረ ልትለኝ ነው! አልናርም!" ብሎ ወደ ሸቀጡ ዞር አለ፡፡

ጨዋታው ጥሞናል፤ ፈገግ አልን፡፡ መለስ አለና፤ "ታስለፈልፉኛላቹ! መቼም የበለፀጋችሁ አይደላቹም አይደል?" አለን፡፡ "እንመስላለን?" ስለው፤ "አይ አትመስሉም፡፡ ቀድሞውኑ እነሱ እዚህ ጭቃማ በረንዳ መምጣት ያቆሙት አምና ከጦርነቱ በፊት ነው፡፡ ደግሞ እናንተ ታዳምጣላቹ፡፡ ወሬ ላይ ቁጥብ ናቹ፡፡ እነሱ እኮ ምላስ" አለ ምላሱን በእጁ እየነካ፡፡

ትንሽ የተማመነን መሰለኝ ቀጠለ፤ "ወላሂ አሁን እኮ እቺ አገር የተወሰኑ ሰዎች አክሲዮን ማሕበር ገብተው የሚነግዱባት የጥቁር ገበያ ነው የምትመስለው፡፡ ልዩነቱ ማን ስንት ድርሻ አለው የሚለው ላይ ነው፡፡ አየህ የአገሪቱን አጠቃላይ ዶላር የሚቸበችቡት ኤርትራውያንና ጥቂት የሰሊጥና የመሬት ዘራፊዎች ናቸው፡፡ ያው እኛ በእነሱ መጀን ነው ያለነው፡፡ ኤርትራውያኑ ከትግራይ ባንኮች ሁሉ የሰበሰቡትንና፤ ከኛው መንግስት ትግራይን ለማጥፋት በቅጥረኛነት የሚከፈላቸውን ብር አዲስ አባባ አምጥተው አጠቃላይ በጥቁር ገበያ ዶላሩን በአደባባይ በሓዋላ እየገዙት ነው፡፡ ትላልቅ ተቋማትን ሳይቀር እየገዙ ነው፡፡ መርሰዲዝ ቤንዘ ካምፓኒውንና ሌሎች ትላልቅ የሰሞኑን ግዥዎች ማን እንደገዛቸው ሂድና አጣራ! ሁሉንም ኤርትራውያን ናቸው የገዟቸው" አለን፤ ፈራ ተባ ማለት ጀምሯል፤ ግራ ቀኙን እየቃኝ፤ ድምፁም እየለሆሰሰ ሄደ፡፡

"እና እነሱ በዶላር እንደዚህ ቢጫወቱ ከዚህ ከምንገዛው ዕቃ ጋር ምን አገናኘው?" አለው ጓደኛዬ፡፡

"አይ ጋሼ፤ እዚህ አገር እኮ ዶላር ሲጨምር፤ ደማካሴ እራሱ ይጨምራል" ከማለቱ፤ ፀጉሩና ሪዙ የተንጨፈረረ፣ በዚህ የነሓሴ ብርዳማ ጭጋግ፤ ሓፍረተ ስጋውና ትከሻው ላይ ብቻ በእራፊ ጨርቅ የሸፈነ፣ ገዘፍ ዘለግ ያለ ጎልማሳ፤ እየለፈለፈ እኛ ወዳለንበት በረንዳ ተጠጋ፡፡

"አዎ! መጥተው ያተራምሱት፣ ይበጥብጡት! እያንዳንድሽ ዓፄ ቴዎድሮስ፣ ዓፄ ቴዎድሮስ የምትጫወቺ፤ ሄደሽ ለማያውቅሽ ታጠኚ! ህዝብን በግፍ እርስ በርሱ ለማጨራረስ፤ ስለምን መይሳውን ትቀሰቅሱታላችሁ!? …ዘራፍ እኔ ለአገሬ ሽጉጥ ካልጠጣሁ ትላለህ! አንድ ጥይት ጦሽ ሲል፤ ቀሚስ ለብሰህ ተኳኩለህ፤ ቋ-ቀጭ እያልክ ልታመልጥ! እናማ የዓፄውን ነፍስ ስለምን ዕረፍት ትነሳለህ?" እያለ አፋጠጠብን፡፡ ጓደኛየ ይሻላል እንጂ፤ እኔማ ብርክ ያዘኝ፡፡ ንክ ሰው አይመቸኝም፤ አንዴ የአራት ኪሎ ዕብድ ማጅራቴን ጨምድዶ አፈር አብልቶኛል፡፡

ጨፈረሩ ሰውየ አጠገባችን እየተንጎራደደ እኛው ላይ እንዳተኮረ ቀጠለ፤ "ተነስ፣ ተነስ ብለህ፤ ይህን በግ ህዝብ በጦርነት ማግደህ፤ ልጆቹን ተራ በተራ አስበልተህ! አገር አውድመህ ትበትናለህ!" እያለ አፍጥጦ እኔው ላይ ጣቱን ቀሰረብኝ፡፡ የፈረደብኝ፤ የልማዴን፤ እንደ አራት ኪሎው ዕብድ ሊነርተኝ ነው እያልኩ፤ ዓይን ዓይኑን አየሁት፤ እየተርበተበትኩ፤ ምነው ልደታየ! ለዚህ ነው ጎትተሽ ጨው በረንዳ ያመጣሽኝ! እያልኩ፤ በውስጤ ነው፤ ድምፅማ ከየት አባቴ ላምጣ፡፡

እንዳፈጠጠብኝ፤ "አንተ ከዚህ ከሞቀው ቤትህ መች ትወጣለህ? ውሃ በሚጠብስ ምላስህ ከሴት ጭን ተወሽቀህ፤ ዓይን ዓይኗን እያየህ፤ ዓይንህን አስለምልመህ፤
አልሄድም ዘመቻ ካንቺ ተነጥዬ፣
አንቺ ጋር ልቀመጥ ቆንጆ ሴት መስዬ፤
እያልክ ትደበቃለህ! በምን አባክ ወኔህ? ሓሞት የታል? አውራ! አውርቶ አዳሪ ሁላ!" ተመስገን ፈጣሪ፤ በፈጣን እርምጃ ትቶን ሄደ፡፡ በነሓሴ ምድር የኬኔተራየ መርጠብ ላብ መሰለኝ፤ የውስጥ ሱሪየን ያራሰው ግን እንጃ፡፡
“አንተ እውነታውን ዘረገፈው አይደል!” አለ ጓደኛ፤ እኔ ስርበተበት እሱ በጣም ተመስጦ ነበር፡፡ "በል እግዚሄር ይስጥህ፤ በልደታ ምድር ጎትተህ አምጥተህ፤ ጉድ አድርገኸኝ ነበር" ስለው፤ "አልሰሜን ግባ በለው" አለ ባለሱቁ፡፡ "ምን ማለት ነው?" አለው ጓደኛዬ፡፡
"ተው አትንካን ቢሉት፣ ነገር ፈለገና፤
ተው አትግባ ቢሉት፣ ጦርነት ገባና፤
ክላሽ ሲንደቀደቅ፣ እመይ ድረሽ አለ ዘራፉ ቀረና።
ገና እነእንትና ለማምለጥ ሙፈሪያትን መስለው የምናይበት ጊዜ ቅርብ ነው፤ ያኔ ‘የ10 ዓመቱን የመንግስት ዕቅድ’ እያስታወስን፤ ቅድም ያላችኋትን ደግመን፤ ‘ከምኔው ከምኔው’ እንላለን! የእኔን ሸቀጥ ‘ከምኔው ከምኔው’ ስትሉ፤ የእነ አሕመድ ሸዴ አዳነች አበቤ እና ሌሎች ባለስልጣናት ቤተሰቦቻቸውን ወደ ዱባይና ሌሎች አገሮች ማሸሽ ግን ‘ከምኔው ከምኔው’ አላለችሁም" ጓደኛየ አፉን ከፍቶ ሲደነቅ፤ እጁን ጎትቸ የቅዳሜ ውሎ ፕሮግራም ሁሉ ተሰርዞ መልስ ወደ ሰፈር፡፡ ለዚህ ለዚህማ፤ አባየ ቤታችን ውስጥ የሚያደርቀኝ መች አነሰኝና!

አዲስ አበቤው ነኝ፤ የነገ ሰው ይበለን!


Post Reply