የአዲስ አበቤው የዛሬ ውሎ - ነሓሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም

Ethiopia related news and publications
Post Reply
africangear
Posts: 404
Joined: Fri Dec 11, 2020 5:07 pm

የአዲስ አበቤው የዛሬ ውሎ - ነሓሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም

Post by africangear »

የአዲስ አበቤው የዛሬ ውሎ
ነሓሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም

ሕልም ነው ቅዠት? አንድ ጥቁር ውሻ ሲያሳድደኝ፤ እኔም ትንሽ ከሸሸሁለት በኋላ፤ መለስ ብየ በቆረጣ መንጋጭላውን ብዬ ከመሬት ስዘርረው ጊዜ፤ አረፋ ደፍቆ፤ ከተጋደመበት ጣረ ሞት እያንዣበበት፤ አንጋጦ የጎሪጥ ሲያዬኝ፤ እኔም ቁልቁል ስመለከተው፤ በውሻኛ ቋንቋ፤ "ዘ...ራ...ፍ!" አይለኝም! ተስፈንጥሬ ብባንን፤ ጨለማው ለብርሃን ቦታውን አስረክቦ፤ የወጋገኑ ጎህ ሲቀድ፤ በበር በመስኮቱ ቀዳዳ ወለል ብሎ ታዬኝ፡፡

ከጥቁር ውሻ ጋር ስሯሯጥ ድምፅ አሰምቼ ነው መሰለኝ፤ አባየ አልጋየ አጠገብ ቆሞ ቁልቁል እያየኝ፤ "ምነው ልጄ፤ እንቅልፍ እምቢ አለክ?" ቢለኝ፤
"አባዬ ዛሬ እኮ፤ የንጉሳችን ልደት ነው፤ መድፍ ተተኮሰ እንዴ?" አልኩት፤ ስለ ቅዠቴ ይሁን ሕልሜ ወሬ የቀየርኩ መስሎኝ፡፡

"ምናባህ ለአገሩ ትንሳዬ ያመጣ መሰለህ እንዴ! ቸነፈር፣ ረሃብ፣ ስደት፣ ጦርነት፣ ዕልቂት፣ ውድመት፣ አንበጣ፣ ወረርሽኝ መቅዘፍት፣ ጭፍጨፋ፣ መዓቱን፣ ኩነኔውን፣ እርግማኑን ሁሉ ይዞ የመጣ ደረቅ ኮቴ፤ ራሱ ምጣት ነው!" አለና ተንፈስ አለ፡፡ ዝርግፍ አድርጎት ወጣለት መሰለኝ፡፡ ቀጠለ፤ "በእርግጥ ካልተኮሳችሁልኝ አይልም አይባልም፤ ግን ደግሞ እነበሎም የዛሬን ዝም ብለው እንዳይውሉ፤ በደብረታቦርና በደባርቅ ግንባር እየተኮሱለት ነው አሉ" አለ ከነፈገግታው፡፡

"አባዬን ግን ሳስብህ የጁንታው ተላላኪ ሳትሆን አትቀርም" ብለው፤ "በሎም…!" አለና በራሴው ትራስ ጠፈጠፈኝ፡፡ አባየ አንዳንድ ቀን ሱሪ በአንገት ነው፤ በዚህ ዕድሜየም እንደህፃንነቴ፤ “ተነስ ልበስ ቤተክርስትያን እንሄዳላን” የሚለውን የዕሑድ አጥቢያ ትእዛዙን አልተወዉም፡፡ “ከዚህ ቤት አልወጣ ስላልኩህ ነው አይደል፤ እንዲህ ሰላም የነሳኸኝ! እንደሰው በሊቢያ ወይ በባህር ልሞክረው? በናንተ ጊዜ እንኳን መጡ ሲባል፤ በቦሌ ወይ በሞያሌ ነበር አሉ” ስለው፤ ይሳሳና ይሸማቀቃል፡፡ እንዲያ ባላሸማቅቀው ትናንትናም ኝኝ ማለቱን ጀምሮኝ ነበር፡፡

ወገኖቼ ቀንም እንዲህ ይጠላል እንዴ፤ ቀኑን እራሱን ለመጥራትም እኮ ነው የተፀየፍኩት! በራሴው ሓሳብና ጊዜ፤ ምንም ነገር ስለውሎየ በትናንትናዋ ቀን እንዳልፅፍ ወስኘ፤ በኔትፍሌክስ የፈረንጁ ፊልም ላይ በቅየ ነበር የዋልኳት፡፡ የዚህን የዕልቂትና ጥፋት መልእክተኛ ሰውየ የምጣት ቀን አስታውሸ፤ በምን አበሳየ እንደካቲካላ ልንተክተክ!

የምጣት ቀኑ ግን ምን አደረገኝ፤ ትሕነግ ነች እነዚህን እንከፍ የማይገሩ አራዊቶች ከየስርቻው ለቃቅማ አደልባ፤ አገር እንዲያጠፉ የለቀቀችብንና፤ ለዚህ ሁሉ ውርደትና ጥፋት የዳረገችን፡፡ ከምር፤ ትሕነግ ግን በሰማይ ቤት ቦታ የለሽም፤ ነፍስሽ አይማርም! ዘንድሮም ስንቱን አባ ዱላ፣ ጁላ፣ ደመቀ፣ ሙፍርያት፣ አብይ፣ አገኘሁ ምናምን… ፈልፍለሽ አራብተሽ አባዝተሽ አደልበሽ ትልኪልን ይሆን! ይህቺ አስለቃሽ የምርኮኛ ሰላምታ ደግሞ ከጩጭየው የምጣት ቀን ኑዛዜ ጋር ተዳምራ፤ “ሽፍታም ሰውን ያሸፍታል” ሲባል አላምንም ነበር፤ ሆነና ከንፈር መጣጩ በዛ፡፡

“በእነ መለስ ጊዜ ከተሜው ጭር ሲል አልወድም ይል ነበር፤ በወቅቱ ደመቅመቅ ያለ ህይወት እየተላመደ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን የተገላቢጦሽ ሆነ“ የጓደኛየ ማኪ እጮኛ ነው፡፡ ምን ለማለት እንደፈለገ አልገባኝም፡፡ ውቃቢየም ስለዚህ ልጅ አልገባህ ብሎት ብዙ ጊዜ ይጠይቀኛል፡፡ ከማኪ ጋር ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ፤ መቐለ ዩኒቨርስቲም አብረን ሄደን፤ የጥንት የሚባል ጓደኛሞች ነን፡፡ ይህ የማይገባኝ ሰውየ የስራ ቦታዋ ተዋውቋትና ተላምዷት፤ ከታጫት ዓመት ሆናቸው፡፡ ማኪ ነች፤ እራሷው እያሽከረከረች፤ አብሬያቸው አዳማ ሂደን የአብዱልጀባርን ለቅሶ እንድንደርስ የለመነችኝ፡፡ ይህ እጮኛ ተብየው ባላበት መኪና ስለምን እያወራን ውለን እንደምንመለስ ሳስበው ተጫጫነኝ፡፡

"እጅን በአፍ የሚያስጭን ገድል የምናበስርበት ጊዜ ቅርብ ነው" በማለት ማኪ የመኪናውን ውስጥ ወሬ ህይወት ዘራችበት፡፡ "ፕሬዝደንት አሽራፍ ጋኒ አፍጋኒስታንን ለታሊባን አስረክበው እስከሸሹበት ሰዓት ድረስ፤ እሳቸውም እንደዚሁ፤ አፍህን አስጭንሃለሁ በሚሉ መግለጫዎች ህዝባቸውን እየጨቀጨቁ ዕረፍት ነስተውት ነበር፡፡ ለካስ ርእሰ ከተማቸው ካቡልን ለታሊባን ማስረከቡ ነበር የአፍ መጫን ሚስጥሩ፡፡ እኛስ አፍ የምንጭነው በምን ይሆን?" አለች በሰፊው ተንፍሳ፡፡

"ሁሉም ሰው የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ እንዲቆም የተባለውስ" አላት ያ እጮኛዋ፤ ስለማታውቁት ነው እንጂ ይህ ሰው ከምር ያስጠላል፡፡

"እሱ እንኳን ያስኬዳል፤ እነበሎም ከእነልጆቻቸው ሳይቀር አምባሳደር ስለሆኑ አይደል እንዴ፤ ዶላሩንም ዲፕሎማሲውንም ያደረቁብን፡፡ አንዳንዴ ከጠላትህም ትምህርት መቅሰም ብልህነት ነው" አለችው በስላቅ፤ ደግ አደረገችው፡፡

"አብዛኞቹ ኢምባሲዎቻችን እየተዘጉ ብዙዎች በዚያው ጥገኝነት እየጠየቁ ነው፡፡ ‘እኛም አገር አለን’ እየዘፈኑ የሚመለሱትን፤ ቦሌ ሲደርሱ ለተመለከታቸው እኮ፤ ተመላሽ ስደተኞች ነው የሚመስሉት" አልኩኝ ማኪን ለማገዝ፡፡
ያ የማይገባኝ ከንፈሩን በአዘኔታ እየመጠጠ፤ "ኦ ማይ ጋድ" አለና፤ ወደ ኋላ ወንበር ዞር ብሎ፤ "የሳውዲ ዓረብ ተመላሾችን እንዳደረገው፤ እነሱንም አዋሽ ወስዶ የጁንታ ምርኮኛ ናቸው እንዳይለን ፋና ወይ ኢቲቪ" ብሎ እንድስቅለት ሲያፈጥብኝ፤ ማኪ ገላገለችኝ፤ እንደማይገባኝም አይገባውም፡፡

"እነ ፋና ስራ በዝቶባቸዋል፤ ሱስ እኮ መጥፎ ነው፤ እንደ ሹካ ማንኪያ፤ የእነበሎምን ፎቶግራፍ ማነሳሳት ጀምረዋል" አለች ማኪ እየሳቀች፤ እንኳን ስቃ ፈገግታዋ እራሱ ቆንጆ ነው፤ እኔም ሳቅኩላት፡፡

ማኪ በእጮኛዋ ላይ ያደረብኝ ስሜት የገባት ይመስለኛል፤ እሱ በተናገረ ቁጥር በመስተዋት አሻግራ እንደምታስተውለኝ እኔም አስተዋልኳት፡፡ ላስቀይማት አልፈልግም፤ ግን የውሸት የማስመሰል ሳቅ እነ አብቹ በገፍ ሲታደሉ እኔ አልነበርኩም፡፡ "መቼም ከትሕነግ የተወረወረበትን ቦንብ በአየር ላይ ተቀብሎ፤ መልሶ በመወርወር አሸባሪውን ደመሰሰው፤ ብሎ የዘገበው የአማራ ብዙሃን መገናኛን ዘገባ የሰማ አዲስ አበቤ፤ ፋናና ኢቲቪ የጁንታውን የድል ፎቶ ሰረቁ ለሚለው ወሬ ብዙም ክብደት አይሰጠውም፤ ስለማይነፋ" አለ፤ የወሬያችን ተቃርኖ ነው፤ ምንድነው አልገባኝም፡፡ እንዲገባኝም አልመኝም!

"ነገ ደግሞ የተወረወረበትን ቦንብ በአየር ላይ ቀልቦ በመዋጥ አመከነ ይሉናል ብለው ነው አዲስ አበቤዎች ሙድ የያዙት" አለች ማኪ፤ ገፅታየን አይታለች፡፡

"ሰራዊትን ለማነቃቃት እንደዚህ ዓይነት ፈጠራዎች ግን አስፈላጊ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በሌለ ተረክ ሞራሉን ማስቆዘርና ለአገር ሉዓላዊነት ማዋጋት" ብሎን እርፍ፡፡ እና ይህ ሰው በእውን ለማኪ የሚገባ ሰው ነው? እራሴን ጠየቅሁ፤ ወንድ ይመስል!
"ጥሎብኝ የመርህ ሰው እወዳለሁ፤ ውሸትን ተፀይፎ ክብርን ንቆ፤ ለህዝቡ መስዋት ለመሆን ሲታገል በእጆቹ ካቴና አጥልቀው መቀመቅ የወረወሩትን! Obbo Baqqalaa Garbaa Baga dhalatte. Dukkanni kun ni bar’’a. Cancalli kunis harka kee irraa ni hiikama!” ከማለቷ፤ "አመጣችው አዘነበችው!" አለ፤ እኔ እንጃ ይህ ሰው ኦሮሞነቷንም የተቀበለው አይመስለኝም፡፡ "ትርጉሙ ይነገረን" አልኳት፡፡

"አጥብቄ የምወደው ኦቦ በቀለ ገርባ ልደቱ ነው፤ ‘መልካም ልደት! ይህም ቀን ያልፋል ይነጋል፣ ያጠለቁብህ ካቴናም ይፈታል’ ነው ያልኩት" አለችኝ፤ በፈገግታዋ አጅባ፤ በመስተዋቱ ውስጥ አሻግራ እያየችኝ፡፡

አዳማ ወዳጃችን ጠበቃ አብዱልጀባር ቤት ደርሰን፤ ባለቤቱን ልጁን መላ ቤተዘመዱን እያፅናናን ዋልን፡፡ አንድ አብዱልጀባር ጋር የነበረንን ትውውቅ የሚያውቅ የቤተሰብ አባል ስለአሰቃቂ ግዲያው፤ ምን ያህል ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እንደነበረ በሐዘን ተውጦ አወጋን፡፡ የአዳማ ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ከቤት ንብረታቸው አባረው ጎዳና ላይ እንደጣሏቸው፤ የንግድ ተቋሞቻቸውን አሽገው ድህነት ውስጥ እንደከተቷቸው፤ በርካቶችም ታስረው እንደተወሰዱ፤ ከተማው የብልፅግና የሽብር መንፈስ እንደተጠናወተው አጫወተን፡፡ አብዱልጀባርም ይህንን የባዕድ ድርጊት አጥብቆ ይቃወም እንደነበር ገለፀልን:: በአገርም እንዲህ ይታዘናል እንዴ! አዘንን አፈርን!

ሐዘን ቤት ብዙ ነገር ቀማምሰን ስለነበር፤ መንገድ ላይ እንቁም፤ ምናምን እንቀማመስ ቢሉኝም፤ ልቤ በሓዘን ስለተሰበረ አሻፈረኝ ብየ፤ ከማይገባኝ ሰው ጋርም ላለመዳረቅ፤ የተኛሁ መስየ ቤቴ በጊዜ ገባሁ!

አዲስ አበቤው ነኝ፤ የነገ ሰው ይበለን!


Post Reply